በምርጫው ያሳየነውን ተሳትፎ በሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ላይ ለመድገም የድርሻችንን እንወጣለን--የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ያሳየነውን ተሳትፎ በሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ላይ ለመድገም የድርሻችንን እንወጣለን--የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች
ሚዛን አማን፣ ግንቦት 27/2017 (ኢዜአ)፡- በምርጫው ያሳዩትን ተሳትፎ በሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ላይ ለመድገም በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ በምርጫው ላይ ያሳየነውን የነቃ ተሳትፎ በልማት ተግባራት ላይ በመድገም ለሀገር ዕድገት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን።
አቶ አህመድ ከድር የተባሉ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ እንዳሉት ምርጫው እኛ ዜጎች ለኢትዮጵያ ከፍታ ያለንን ጽኑ ፍላጎትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መከበር ያለንን አቋም ያሳየንበት ነው።
በምርጫው ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የሌት ቁር የቀን ሀሩር ሳይበግረን ተግባራችንን እንደተወጣን ሁሉ በቀጣይም ለሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
ወይዘሮ ሰዋለም ጋሻው በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ በምርጫ ወቅት ያሳየው ንቁ ተሳትፎ በልማት ሊደግም እንደሚገባው ገልጸው ፓርቲዎችም የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን በፀጋ መቀበል እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
በምርጫ ወቅት ያሳየነውን የነቃ ተሳትፎ በሌሎች የልማት ሥራዎች በመድገም ለኢትዮጵያ ከፍታና አሸናፊነት እንሰራለን ያሉት ደግሞ መምህር መንዛ ዝትያብ (ዶ/ር) ናቸው።
እንደ ሀገር አይቻልም የተባሉ በርካታ ጉዳዮችን በኢትዮጵያዊ ወኔና የአይበገሬነት መንፈስ እየቻልን አሳይተናል፤ በምርጫውም ይህንኑ ደግመናል፤ በልማቱ ደግሞ የተጀመሩ ጥረቶችን በትብብር እናጠናክራለን ብለዋል።
ወጣት ዘማች ዳሩ በበኩሉ በራሳችን ፍላጎትና ተነሳሽነት በመምረጥ የዜግነት ግዴታችንን መወጣታችን ለዴሞክራሲ ባህል ማደግ ትልቅ ትርጉም አለው ሲል ገልጿል።
በቀጣይም ለልማትና ዕድገታችን በጋራ በመንቀሳቀስ ለሰላማችን፣ ለልማትና የኑሮ ውድነት ተፅዕኖን ለመቀነስ ተግተን በመሥራት ለኢትዮጵያ ክብር በብርታት እንቆማለን ብሏል።