ጠቅላላ ምርጫው ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ የተጠቀሙበት ነው - የጋራ ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላላ ምርጫው ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ የተጠቀሙበት ነው - የጋራ ምክር ቤቱ
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ የተጠቀሙበት መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለፀ።
የጋራ ምክር ቤቱ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የምክር ቤቱ ተሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ እንደተናገሩት፤ በምርጫው ወቅት መራጩ ህዝብ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ድምፁን መስጠት መቻሉ የዘንድሮውን ሂደት ከሌሎች ወቅቶች የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
ምርጫው ሕዝቡ ከማለዳው ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን የሰጠበት መሆኑን አንስዋል።
ህዝቡ በምርጫው ወቅት ያሳየው ቁርጠኝነት፣ የሀገር ማጽናት ጉዞውን እውን ለማድረግ ያለምንም እንከን እና በተረጋጋ ስሜት የፈለገውን ፓርቲ በፍትሃዊነት የመረጠበት መሆኑን ምክር ቤቱ ማረጋገጡንም አቶ ጎበዜ አክለው ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወደፊት ይፋ የሚደረገውን የምርጫ ውጤት በፀጋ እንደሚቀበልና ከሚመሰረተው መንግስት ጋርም በሀገር ሰላምና ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በምርጫው የጋራ ምክር ቤቱ ተቀናጅቶ በመስራቱ እና መራጩ ህዝብ ሀገር ለማስቀጠል ያሳየው ቆራጥነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ለምርጫው ሰላማዊነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝቡ የዴሞክራሲያዊ ባህል የዳበረበት መሆኑን እንዳሳየ የተናገሩት ደግሞ የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሻጌ ሻምባ ናቸዉ።
ህዝቡ ለፈለገዉ ፓርቲ ድምጽ በመስጠት ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሚናውን መወጣቱንም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያቀርቡ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታና ሰፊ ምህዳር ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ ፀሐፊ አቶ ወልዴ ዳና በበኩላቸው ሕዝቡ ድምጹን ለፈለገው ፓርቲ በመስጠት የስልጣን ባለቤትነቱን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።