ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አህጉራዊ የማይበገር የጤና ስርዓትን ለመገንባት መሪ ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች-ዶክተር ደረጀ ዱጉማ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ  አህጉራዊ የማይበገር የጤና ስርዓትን ለመገንባት መሪ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተምሳሌታዊ ስኬቶች በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።

የአፍሪካ  በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ከጤና ሚኒስቴርና ከአህጉራዊ  የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር በአፍሪካ የጤና ደህንነትና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ላይ ያተኮረ አህጉራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምክክሩ ዋና ዓላማ የአፍሪካ ሀገራት የቅድመ በሽታ መከላከል አቅምን ለማሳደግ ትብብራቸውን ለማጠናከር ነው።

ቅድመ በሽታ መከላከል ለኢትዮጵያ የጤና ስርዓት የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን በማንሳት፥ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሻሻለውና በተለይ ደግሞ በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ለዚህ ውጤት መገኘት ከመንግስት ቁርጠኝነት በተጨማሪ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የአጋር አካላት ትበብር ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከቅድመ በሽታ መከላከል ባሻገር አክሞ የማዳን አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በራስ አቅም በመቆጣጠር ረገድ አድናቆትን ያተረፉ ተግባራትን ማከናወኗን ጠቁመዋል።

አፍሪካውያን የበሽታ ቅድመ መከላከልን ጨምሮ የጤና ደህንነትን በማረጋገጥ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት እርስ በርስ መተባበር እንዳለባቸው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ያላትን የበሽታ ቅደመ መከላከል ልምድ በማካፈል አህጉራዊ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት መሪ ሚናዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።


 

የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ራጂ ታጁዲን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በተለይ በበሽታ ቅድመ መከላከል ላይ ትበብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው በማንሳት፥ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከሉ  ትብብሩን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም