በአማራ ክልል ከ8 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ8 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይከናወናል
ባህርዳር፣ግንቦት 27 /2018 (ኢዜአ):-በአማራ ክልል ከ8 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚከናወን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ተግባራት ይከናወናሉ።
እነዚህም የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት መገንባትና ማደስ፣ ማሳን በዘር በመሸፈን፣ ችግኝ በመትከል፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ደም መለገስና ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ወጣቶች የሰላም ባለቤት እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ፤ በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም ህብረተሰቡን በጉልበቱ፣ በእውቀቱና በገንዘቡ 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን በማከናወን 15 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር፣ አንድነትን ብሎም የመረዳዳት እሴቶችን በማሳደግና የመንግስትን የልማት ክፍተቶች በመሙላት ረገድ የራሱ አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም ወጣቱም እውቀቱን፣ ጉልበቱንና ጊዜውን ለሃገር ግንባታ እንዲያውል በማድረግ ያበረከተው አስተዋጽኦ ዜጎች ለሃገራቸው ያላቸውን የባለቤትነትና የተቆርቋሪነት ስሜት እየጎለበተ እንዲመጣ ያስችላል ሲሉም አክለዋል።
በአገልግሎቱ የሚሰማሩ ወጣቶችም የመተባበርና አብሮ የመስራት ባህልን ከማሳደግ ባሻገር የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግና እሴት ለመገንዘብ እድል እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።
ተግባሩ በአገልግሎቱ የሚሳተፉ ወጣቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ቀድሞ በመለየት ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ እስከ መስከረም ወር አጋማሽ ድረስ ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፤ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎችን በማሳተፍ ከ15 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።