የባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከጣና ውበት ጋር በማሰናሰል የተገነባ ዘመን ተሻጋሪ የቱሪዝም ሃብት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከጣና ውበት ጋር በማሰናሰል የተገነባ ዘመን ተሻጋሪ የቱሪዝም ሃብት ነው
ባህር ዳር ፤ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ) ፡-የባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከጣና ውበት ጋር በማሰናሰል የተገነባ ዘመን ተሻጋሪ የቱሪዝም ሃብት መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከተማዋ በተፈጥሮ የታደለችና አባይና ጣናን ተንተርሳ መመስረቷ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ይበልጥ ውበቷ እየተገለጠ እንድትመጣ አድርጓታል።
የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ትዕግስት አበጀ፤ ባህር ዳር ከተማ በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት አመታት ደግሞ ውበቷን የገለጡ የልማት ስራዎች መከናወናቸው ውበቷን ያጎላው መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ ከኮሪደር ልማቱ በተጨማሪ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው ውበቷና ድምቀቷ ይበልጥ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
የባህር ዳር የኮሪደር ልማት ከጣና ሃይቅ ጋር በተሳሰረ መልኩ የተገነባ መሆኑም ከተማዋን ልዩ ገፅታ ስለማጎናፀፉ አንስተዋል።
እንደ አጠቃላይ የባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከጣና ውበት ጋር በማሰናሰል የተገነባ ዘመን ተሻጋሪ የቱሪዝም ሃብት መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ደጀኔ አለምነው፤ የባህር ዳር ውበትና የቱሪዝም መስህብነት ከእለት ወደ እለት እያደገ መሆኑን ተናግሯል።
በከተማዋ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ፣ የሳይክል መንገዶችና ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶች መዘጋጀታቸው ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለቱሪስቶች ምቹ አድርጓታል ብሏል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ገብረስላሴ ሳህሌ፤ ከባህር ዳር ከተማ ለዘመናት ተከልሎ የነበረው የጣና ሃይቅ ውበት በኮሪደር ልማት መገለጡ ለነዋሪዎችም ይሁን ለጎብኝው ደስታ ፈጥሯል ብለዋል።
አሁን ላይ ወደ ባህር ዳር ጎራ የሚል ሁሉ ከተማዋን እየጎበኙ የጣናን ውበት እያደነቁ የሚደሰቱበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በባህር ዳር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎችም የተገነቡ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።