ቀጥታ፡

የረቀቁ የአበረታች ቅመሞች አጠቃቀም ስልቶችን ለመከላከል የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየተገነባ ነው-ባለስልጣኑ

አዳማ፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፦ የረቀቁ የአበረታች ቅመሞች አጠቃቀም እና የማጭበርበር ስልቶችን ለመግታት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየተገነባ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በስፖርት ውስጥ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞች (Doping) እና ዘዴዎች አስመልክቶ ለስፖርት ጋዜጠኞች ያዘጋጀው የስልጠናና የውይይት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

መድረኩ ባለስልጣኑ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞች (Doping) እና ዘዴዎች የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራ ይበልጥ ውጤታማ እና ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነው ባለው ስራ የስፖርት ጋዜጠኞች ያላቸውን ሚና ማሳደግን ያለመ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል የስፖርት ጋዜጠኞች በአበረታች ቅመሞች ዙሪያ የስፖርት ማህረሰቡን እና የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በመፍጠር ውጤታማ ስራዎችን መስራት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የፀረ አበረታች ቅመሞች ስራ ከሚዲያ ስራ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ጠቅሰው፥ በዚህ ረገድም ሚዲያ የማይተካ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በአበረታች ቅመሞች ዙሪያ ባለፉት ዓመታት ሚዲያው ተግቶ ሲሰራ መቆየቱንና የአመላካከት ለውጥ እየመጣ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ከነበረበት ችግር ወጥቶ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ተቋማዊ አቅም በመገንባት በአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

የፀረ አበረታች ቅመሞች ስራ የበለጠ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እየታገዘ እንደሚገኝና ባለስልጣኑም ከወቅቱ ጋር በመራመድ ተቋማዊ ብቃቱንና የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የአበረታች ቅመሞች በስርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተትና በስፖርት እና የስልጠና ማዕከላት ተከታታይ ግንዛቤ መፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ በመሆናቸው በዘላቂነት ውጤት እንደሚያመጡ ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ የምርምር እና የቁጥጥር አቅሙ መጨመሩን እያሳደገ እንደሚገኝና ህገ ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አትሌቶች እና ሌሎች አካላት ላይ የህግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የምርምር እና ቁጥጥር ተሞክሮ እና ውጤቶች ማስፋት እና ማጠናከር እንደሚገባም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

የፀረ አበረታች ቅመሞች የመከላከል እና የመቆጣጠር አቅም ማደግ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ፣ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት ለማሳደግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎን ለማረጋገጥ የፀረ አበረታች ቅመሞች መመዘኛዎች ማሟላት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የስፖርት ፍትሃዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቅሰው፥ አትሌቶች ሙያ፣ ተፈጥሯዊ ጥረት እና አቅም በመጠቀም ውጤት ለማምጣት መስራት አለባቸው ብለዋል።

የስፖርቱን ተአማኒነት ለማጽናት እና ለማስቀጠል የፀረ አበረታች ቅመሞች ስራ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

አትሌቶች እና ዜጎች ከጤና፣ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ችግሮችና ቀውሶች ለመጠበቅ የቁጥጥርና የምርመራ ስራውን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነም አንስተዋል።

የአበረታች ቅመሞች አጠቃቀም በቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ታግዘው እየረቀቁ መምጣታቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከጊዜው ጋር የሚሄድ ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ አቅም ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድም መገናኛ ብዙሃን የተከለከሉ አበረታች ቅመሞች መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ያላቸውን ግንዛቤ መፍጠር እና የአመለካከት ለውጥ የማምጣት ስራ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ ዶፒንግ ፤ የጋዜጠኞች ስነ ምግባር፤ የአበረታች ቅመሞች ፅንሰ ሀሳቦች፣ ዓለም አቀፍ የዶፒንግ ተጽእኖና የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን እንቅስቃሴ በሚሉ ጉዳዮች ላይ የመወያያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በሀገራችን ስፖርት ውስጥ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞች (Doping) እና ዘዴዎች የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 ስልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመ የፌዴራል ተቋም ሲሆን ባለፉት 8 ዓመታት በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል ህብረተሰቡንና የስፖርቱን ቤተሰብ በስፋት ለማንቃት የተጠናከሩ የሚዲያ ንቅናቄ ፕሮግራሞችን በተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም