የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎች ሽግግርን እያጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎች ሽግግርን እያጠናከረ ነው
ሐረር፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ) ፡-የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት መለዋወጥን መቋቋም በሚችሉና ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ የግብርና ምርቶች ላይ የሚያከናውነውን የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝዳንት ይስሃቅ ዩስፍ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር አብሮ የሚሄዱ የሰብል ዝርያዎችና የእንስሳት እርባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም በየአካባቢው የሚከሰተውን ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ሁኔታ ተቋቁመው የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ አዳዲስ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ለህብረተሰቡና ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት እንዲሁም የማስፋት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት በዘንድሮው ዓመት ብቻ የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁመው ምርት መስጠት የሚችሉ 120 ነባርና አዳዲስ የግብርና ውጤቶችን ለማህበረሰቡ ማዳረስ መቻሉን ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በጤና እና ቴክኖሎጂዎች ላይም እየሰራና እውቅና እያገኘ እንደሚገኝም አክለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ ረገድ የአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚና ወጪ ቆጣቢ፣ ምቹ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር የማፍለቅ ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የዕጽዋት ሳይንስ መምህርና የግብርና ምርምር ትኩረት መስክ አስተባባሪ ዮናስ ሞገስ(ዶ/ር)፤ የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና በምርትና ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ጎልቶ እንደሚስተዋል ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን መስራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት ድርቅን ተቋቁመው ምርት የሚሰጡ ሁለት የለውዝ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ዝናብ አጠር አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የማሰራጨት ስራ ማከናወኑን አንስተዋል።
ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ሊቋቋሙ የሚችሉ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች ላይም ምርምሮችን በማከናወን ለተጠቃሚው የማዳረስና የማስፋት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ዘርፍም አዳዲስና የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ የምርምር ስራዎችን እያወጣ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ መምህርና ተመራማሪ ኢንጅነር ሃምዛ አህመድኑር ናቸው።
በተለይም በአካባቢው በሚገኙና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቁሶችን ተጠቅሞ የመኖሪያ ቤት መገንባት የሚያስችል የምርምር ስራ ማከናወኑን የገለጹት ኢንጅነር ሃምዛ፤ ይህም እንደ ሀገር ተቀባይነት ማግኘቱንና የማስፋት ስራውም እየተከናወነ መሆኑን አክለዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 43ኛው ዓመታዊ የምርምርና የማህበረሰብ ተሳትፎ ግምገማ ጉባዔውን ሰሞኑን ማካሄዱ ይታወሳል።