በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ መሠረተ ልማቶች ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ መሠረተ ልማቶች ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም እየሆኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፦በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የጥራት ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም እየሆኑ መምጣቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ጤና ለመጠበቅና ፍትሐዊ የሕክምና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አዲስ የተሻሻለ የጤና ፖሊሲ ሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን ይህም በሽታን መከላከልና የአክሞ ማዳን አገልግሎት መስጠት ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት እና የእንቅስቃሴ ውስንነት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በእጅጉ እንዲጨምሩ ምክንያት ሆኗል።
መሆኑም በሽታዎቹን በተለያዩ ደረጃዎች ቀድሞ መለየትና አክሞ የማዳን አቅምን በዚያው ልክ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አዲሱ የአክሞ ማዳን ፖሊሲ በትኩረት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
አዲሱን ፖሊሲ ተከትሎ በሁሉም ደረጃ በሚገኙ የጤና ተቋማት የተሟላ የሕክምና ግብዓት እንዲሁም የሠለጠነ የሰው ኃይል በቁጥርም ሆነ በስብጥር እንዲኖራቸው በማድረግ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም አስታውቀዋል።
ትላልቅ ሆስፒታሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው ሆስፒታሎቹ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ የማይሰጡ የላቁ የሕክምና አገልግሎቶችን በስፋት መስጠት መጀመራቸውን አብራርተዋል።
ይህ ስኬት የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ዜጎችን ቁጥር ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ውጤታማ ለማድረግ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በመንግስትም በግሉ ዘርፍ ትላልቅ ሆስፒታሎች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ አቅም ማምረት ለዘርፉ ዘላቂ ስኬት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህ ረገድ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ በርካታ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ከሰባት ዓመታት በፊት መድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎችን በራስ የማምረት አቅም ከነበረበት ዝቅተኛ የ8 በመቶ ደረጃ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 44 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ይፋ አድርገዋል።
በቀጣይም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ይበልጥ በማጠናከር ይህንን የማምረት አቅም ወደ 60 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።