7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መመዘኛዎች ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ የምርጫ ሂደት ነው- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መመዘኛዎች ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ የምርጫ ሂደት ነው- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ቦንጋ፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መመዘኛዎች ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ የምርጫ ሂደት መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ።
አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱንና የዜጎችን ተሳትፎ በተመለከተ የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም የምርጫ ሂደቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ በርካታ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በሃሳብ ክርክር የዘለቀና ድምፅ ለመስጠትም በርካታ ዜጎች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።
በድምጽ አሰጣጡም ዜጎች ዝናብ፣ ብርድና ፀሃይ ሳይበግራቸው ከማለዳ እስከ ሌሊት ድምፅ የሰጡበት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉንም አሳታፊ ባደረገ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ምክር ቤቱ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አንስተው በዚሁ መልኩ መከናወኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ምርጫው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደቱ እንደ አጠቃላይ የተሳካ መሆኑን ገልጸው በፖለቲካ መፎካከሩ እንዳለ ሆኑ በቀጣይ ሀገርን በመገንባት ሂደት በጋራ መቆም ይኖርብናል ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ኢትዮጵያውያን ከማለዳ እስከ ምሽት በከፍተኛ ተነሳሽነት ድምፅ መስጠታቸው የሚደነቅ መሆኑን መግለፃቸው ይታወቃል።
የህብረቱ የታዛቢዎች ቡድንም በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ምርጫውን በአግባቡ መከታተሉን ገልጸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሟላ ዝግጅትና በህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ ምርጫው በስኬት የተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፎካከሩበትና 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡበት ታሪካዊ ምርጫ መሆኑ ይታወቃል።