ቀጥታ፡

በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማዋን እንቅስቃሴ አቀላጥፏል

አሶሳ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የትራፊክ ፍሰትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት፤ የከተማዋን መሠረተ ልማት ለማዘመን፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ከተማዋን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ሳቢ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረ ሰፊ መርሃ ግብር ነው። 

በአንደኛው ዙር የተከናወኑት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተከትሎ፣ አሁን ላይ ትኩረቱን የንግድና ማህበራዊ አገልግሎት ማዕከላትን ማዘመን ላይ ያደረገው ሁለተኛው ዙር ስራ በስፋት እየተገነባ ይገኛል።

የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት፣ ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ብቻ ሳይሆን ምቹ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶችንም በማካተት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ይገኛል።

አስተያየታቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገዱ ተለይቶ መሰራቱ የትራፊክ ፍሰቱን በእጅጉ አቅልሎታል።


 

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ማስረሻው አራጌ እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም የነበረው መንገድ ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ለተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኞች ምቹ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን በኮሪደር ልማቱ ለሁሉም ምቹ መንገድ በመፈጠሩ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴው መሳለጡን አቶ ማስረሻው ተናግረዋል።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ የሺወርቅ ንብረት፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን በሁሉም መስክ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል።


 

በተለይም በሁለተኛው ዙር እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት፣ በእግረኞች ላይ ይደርስ የነበረውን የትራፊክ አደጋ በመቀነስ ረገድ አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በከተማዋ የባጃጅ አሽከርካሪ የሆነው አህመድ ሰኢድ በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ ለአሸከርካሪዎች ነፃነትን የሰጠ እና ለተሽከርካሪዎችም ምቹ መሆኑን ተናግሯል።


 

የኮሪደር ልማቱ ለአሸከርካሪዎች እና እግረኞች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ደግሞ በአሶሳ ከተማ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ምክትል ሳጅን ኢዘዲን አልበሽር ናቸው።


 

የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን የሥራ ጫና የቀነሰ እና የተቀላጠፈ የትራፊክ እንቅሰቃሴ እንዲፈጠር አይነተኛ ሚና ያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም