ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የጊዜያዊ ውጤቶች ይፋ ተደርገዋል -ምርጫ ቦርድ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የጊዜያዊ ውጤቶች ይፋ ተደርገዋል -ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የጊዜያዊ ውጤቶች ይፋ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ገለጹ።
ሰብሳቢዋ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል።
ሰብሳቢዋ እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት ከየምርጫ ጣቢያዎቹ ወደ ምርጫ ክልል የደረሱ ውጤቶችን የመደመር ሥራ በምርጫ ክልል ደረጃ በጥንቃቄ እየተከናወነ ይገኛል።
ይህም ውጤቶቹን የመደመር ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም፣ ውጤቱ በቀጥታ ወደ ዋናው ማዕከል የሚላክ መሆኑን ሰብሳቢዋ አብራርተዋል።
በምርጫው የተሳፉ ዜጎች ብዛት በተመለከተም፣ አጠቃላይ ውጤት ከክልሎች ተጠቃሎ ሲመጣ ቦርዱ ይፋ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
ሰብሳቢዋ አክለውም ዛሬ የተወሰኑ ምርጫ ክልሎች ላይ የመደመር ስራዎች ተጠናቆ ወደ ማዕከል እየተላኩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ውጤቶች በአብዛኛው መለጠፉን ጠቁመው፤ በዚህም በምርጫ ቅጽ ላይ ትክክለኛነቱን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫ ክልሎች ስፋት መሰረት የተለያየ ቡድን ያሉበት የማጣሪያና የውጤት ማረጋገጫ ቡድን ተቋቁሞ በዛሬው እለት ቡድኖቹ በድጋሜ ስልጠና ሲሰጣቸው መዋሉን ገልጸዋል።
እነዚህም ከየምርጫ ክልሉ እና ጣቢያዎች ውጤቶችን የማናበብ እና የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ውጤቶቹን የመደመር ስራ በየምርጫ ክልሎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ቆጠራ የጨረሱት ደግሞ ወደ ማዕከል እየተጓጓዙ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ የማጠቃለያ ውጤት በሂደት ተረጋግጦ ውጤቶች በሂደት የሚገለጽ ይሆናል ብለዋል።