ህብረት ለምርጫ በታዘበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ህብረተሰቡ በንቃት የተሳተፈበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህብረት ለምርጫ በታዘበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ህብረተሰቡ በንቃት የተሳተፈበት ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ በታዘበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ የታየበትና ሰላማዊ መሆኑን ገለፀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህ ወቅት የኅብረቱ የቦርድ ሰብሳቢ ሳህለሥላሴ አበበ፤ ኀብረቱ ለምርጫ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከሦስት ሺህ በላይ ተቀማጭና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን አሰማርቷል።
ህብረት ለምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ትዝብት ሪፖርቱ የህብረት ለምርጫ ታዛቢዎች በድምፅ መስጫ ቀን በተሰማሩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በታዘቧቸው ሂደቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ተናግረዋል።
ህብረት ለምርጫ ከታዘባቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች 99 በመቶዎቹ በህግ በተፈቀዱ ቦታዎች መቋቋማቸውን፣ ከቦርዱ እውቅና የተሰጣቸው ታዛቢዎች ያለምንም ገደብ ወደ ጣቢያዎች ገብተው መታዘብ መቻላቸውን ተመልክቷል ብለዋል።
የህብረት ለምርጫ ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያ ሲደርሱ የምርጫ አስፈፃሚዎች በቦታው መገኘታቸውን፣ በሁሉም ጣቢያ የምርጫ ድምጽ መስጫ ሳጥኖች ከመታሸጋቸው በፊት ባዶ መሆናቸውን መታዘባቸውንም አክለዋል።
የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ የቦርዱ ህጋዊ ማህተም፣ የማይለቅ የጣት ቀለም፣ የመራጮች መዝገብ፣ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች በሁሉም ጣቢያዎች መሟላታቸውንም መታዘባቸውን ገልፀዋል።
የድምፅ መስጫ ጣቢያዎቹ ለሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መራጮች ምቹ እንደነበሩም መታዘባቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከመራጭነት ምዝገባ እስከ ድምፅ መስጠት ባለው ሂደት የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ የታየበት እና ሰላማዊ እንደነበር ገልፀዋል።