ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሚቀጥሉት ቀናት ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል።

እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ያመላክታል።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች እና የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም አስታውቋል።

በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።

በሌላ በኩል በተለይም የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በአፋር ክልል፣ በሰሜንና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከ32 እስከ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ይሆናል።

በመደበኛ ሁኔታ ወቅታዊው የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚጀምር ሲሆን፤ በሂደት እየተጠናከረ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚስፋፋም ገልጿል።

በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በመካከለኛውና በምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ዝናቡ በመጠንም ሆነ በስርጭት የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃል ብሏል።

የሚኖረው እርጥበት ለግብርና ስራ የማሳ ዝግጅት እና የመኸር ሰብሎችን ለመዝራት እንዲሁም ለበልግ ሰብል ተጠቃሚ አካባቢዎች መልካም አጋጣሚ እንደሚኖረው ጠቁሟል።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የአገሪቱ ተፋሰሶች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው የገጽምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል።

በዚህም በመካከለኛው እና ታችኛው አባይ፣ ላይኛው እና መካከለኛ ባሮ አኮቦ፣ ላይኛው ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ፣ አዋሽ እንዲሁም ገናሌ ዳዋ ከመካከለኛ እስከ ከባድ የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት ይኖራቸዋል ብሏል።

በላይኛው አባይ፣ ኦጋዴን፣ መካከለኛው አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ እና ኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸውም ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም