የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ እንደሚያካሂድ ተገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስብሰባው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በዓለምዓቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶች ለማፅደቅ የወጡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥትና እና በሴራሊዮን ሪፐብሊክ መንግሥት፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በአንጎላ ሪፐብሊክ መንግሥት፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በባንግላዲሽ ሕዝባዊ ረፐብሊክ መንግሥት፤ እንዲሁም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያጸድቅ ተገልጿል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
በተያያዘም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሻል የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያጸድቅ ተገልጿል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን፣ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅን፣ የምግብ ስርዓትና ስርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅን ፣ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን እና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች እንደሚመራም ተመላክቷል።