ቀጥታ፡

የምርጫ ሂደቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥሩ መሰረት እየያዘ መሆኑን የተመለከትንበት ነው - የጋራ ምክር ቤቱ

ሰመራ፤ ግንቦት 26/2018 (ኢዜአ)፡- የምርጫ ሂደቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥሩ መሰረት እየያዘ መሆኑን የተመለከትንበት ነው ሲል የአፋር ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የጋራ ምክር ቤቱ እንደገለጸው፤ በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ ታይቶበት በሰላምና በተሳካ ሁኔታ የተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ እና የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር ሐንፍሬ አሊሚራህ፤ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ያለመታከት ህዝቡ ድምፅ በመስጠት ያደረገውን የነቃ ተሳትፎ አድንቀዋል።

አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥሩ መሰረት እየያዘ መሆኑን የተመለከትንበት ነው ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባል እና የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ መሐመድ ዳውድ በበኩላቸው፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ በሆነ መልኩ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፎካከሩበትና 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡበት ታሪካዊ ምርጫ መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ፤ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስኬት የተጠናቀቀ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም