ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ለአህጉራዊ አጀንዳዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች -አምባሳደር ለምለም ፍስሃ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ለአህጉራዊ አጀንዳዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች -አምባሳደር ለምለም ፍስሃ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ለአህጉራዊ አጀንዳዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደር ለምለም ፍስሃ ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ አዲስ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙትን የአምባሳደር ለምለም ፍስሃ የሹመት ደብዳቤ ዛሬ ተቀብለዋል።
ሊቀመንበሩ ለአምባሳደር ለምለም ፍስሃ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የአምባሳደሯ ልምድና አመራር በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለህብረቱ እያደረገች ያለውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደነቁት ሊቀመንበሩ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ሰላማዊና ሥርዓቱን ጠብቆ በመካሄዱ አድንቀዋል።
ሁለቱ ወገኖች በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች እንዲሁም በህብረቱ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ሃሳብ የተለዋወጡ ሲሆን፤ ሊቀመንበሩ የህብረቱን ግቦች ለማሳካትና በአህጉሪቱ የሚጋረጡ ፈተናዎችን ለመመከት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ለምለም ፍስሃ በበኩላቸው የሊቀመንበሩን አመራር ሰጪነት አድንቀው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ለአህጉራዊ አጀንዳዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት መግለጻቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።