ቀጥታ፡

ምርጫው የህብረተሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እና የዴሞክራሲ ልምምድ እየጎለበተ መምጣቱ የታየበት ነው 

ሆሳዕና፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የህብረተሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማደጉንና የዴሞክራሲ ልምምዱ እየጎለበተ መምጣቱን በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። 

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የተካሄደ መሆኑን በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በተሟላ ዝግጅት ምርጫውን የመራበት፣ ያስተባበረበትና ያስፈፀመበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑም ተገልጿል።

በምርጫው ሂደትና የህዝብ ተሳትፎ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደገለጹት፤ ምርጫው የህብረተሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እና የዴሞክራሲ ልምምዱ እየጎለበተ መምጣቱን በተግባር ያሳየ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሰብዕና ግንባታ ምክትል ዲንና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ዳንኤል ሀንዲኖ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ዜጎች በምርጫ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ምርጫ ካርድ ከመውሰድ ጀምሮ እስከ ድምፅ መስጠቱ ድረስ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተስተዋለው የማህበረሰቡ ተሳትፎ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምርጫዎች የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

የጠቅላላ ምርጫው ሂደት የማህበረሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እና የፖለቲካ ልምምዱ እያደገ መምጣቱን ከማሳየት ባለፈ  ህዝቡ የስልጣን ባለቤት ራሱ መሆኑን በተጨባጭ ያረጋገጠበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በምርጫው አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ወደ ስልጣን ከሚመጣው አካል ጋር በትብብር የሀገረ መንግስት ግንባታውን ማጠናከር እንደሚገባም ዳንኤል (ዶ/ር) አክለዋል።

ለእዚህም ማህበረሰቡ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ያሳየውን የነቃ ተሳትፎ ሀገራዊ ልማትን ለማስቀጠል በሚደረጉ ጥረቶች  ማስቀጠል እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሙላለም ሀይለማርያም በበኩላቸው፤ ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለሀገር ቀጣይ እጣ ፈንታ የተሻለ ውሳኔ የሚሰጡበት ነው።

የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ለብርድና ለፀሐይ ሳይበገር ይሆነኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን በነጻነት በመስጠት ንቁ ተሳትፎ ያደረገበት እንደነበረም ተናግረዋል።

ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ የዴሞክራሲ ልምምድ እየጎለበተ መምጣቱን ያመላከተና ህዝቡ የስልጣን ባለቤትነቱን በተጨባጭ ያረጋገጠበት ስለመሆኑ በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

በጠቅላላ ምርጫው ህብረተሰቡ በድምጹ የሚፈልገውን መሪ የመሰየምና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የመጠቀም ልምምዱን ማጠናከሩንም አመልክተዋል።

በምርጫ ከህዝብ ይሁንታ ውጪ በሌላ አማራጭ ወደ ስልጣን ለመምጣት ለሚፈልጉ ሌሎች አካላትም ህዝቡ ምላሽ የሰጠበት ምርጫ መካሄዱን ገልጸው፣ የምርጫው ሂደት ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር ተሞክሮ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም