ቀጥታ፡

በምርጫው ወቅት ያደረግነውን ንቁ ተሳትፎ በልማትም ለመድገም ዝግጁ ነን 

ቦንጋ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ በምርጫው ወቅት ያደረጉትን ንቁ ተሳትፎ በሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይም ለመድገም መዘጋጀታቸውን የቦንጋ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅን አስመልክቶ ኢዜአ የቦንጋ ከተማ ወጣቶችን አነጋግሯል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች እንዳሉት ህዝቡ በምርጫው ቀን ድምጹን በመስጠት ያሳየው ቁርጠኝነት በኢትዮጵያ ስልጣን በምርጫ ብቻ መያዝ እንዳለበት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያረጋገጠ ነው፡፡

ወጣት አዛሪያስ አየለ፤ ዜጎች በምርጫ ካርዳቸው በቀጣይ የሚመራቸውን መንግስት ለመወሰን ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ማሳየታቸውን ገልጾ፤ ይህም በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርአት እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል ብሏል።

ህዝቡ መሪዎቹን በመምረጥ ለምርጫው ስኬት ያሳየውን ትጋት በቀጣይም በሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበትና እሱም ለዚህ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ይህም በምርጫው የህዝብ ይሁንታ በማግኘት መንግስት የሚመሰርተው አካል ወጣቱ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትጋት መስራት እንዳለበት ገልጿል።

ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ይመራኛል ላለው ድምጹን መስጠቱንና በቀጣይም የመሪውን ውሳኔ በተግባር ማዋሉ የህብረተሰቡ የዴሞክራሲ ባህል ልምምድ እንዲዳብር ያደርጋል ያለው ደግሞ ወጣት አንሙት ወርቁ ነው፡፡

የህዝቡ ንቁ ተሳትፎ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የራሱ ድርሻ እንዳለው ገልጾ፣ በምርጫው ያሳየውን ንቁ ተሳትፎ በቀጣይም ከሚመረጠው መንግስት ጋር ተባብሮ በመስራት እንደሚደግመው ተናግሯል።

በድምጽ አሰጣጥ ወቅት የታየው የህዝብ ተሳትፎ ስልጣን ከምርጫ ውጪ በሌላ መንገድ መያዝ እንደማይቻልና ህዝቡም ፍላጎቱ ይህው መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት አዲሱ አበበ የተባለ የከተማዋ ነዋሪ ነው።

አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ሕዝብ ለሰላምና ለልማት ቁርጠኛ ከሆነ ከመንግስት ጋር በተባበረ ክንድ በመስራት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ተባባሪቱን እንደሚያሳይ ገልጿል።

በምርጫው የሚያሸንፍ ፓርቲ በሚመሰርተው መንግስት በተላይ ወጣቱን ማሳተፍና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባው ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም