በምርጫው የድምጽ መስጫ እለት የታየው የነቃ የህዝብ ተሳትፎ የመንግስት ስልጣን በምርጫ ብቻ መሆን እንዳለበት ትምህርት የሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው የድምጽ መስጫ እለት የታየው የነቃ የህዝብ ተሳትፎ የመንግስት ስልጣን በምርጫ ብቻ መሆን እንዳለበት ትምህርት የሰጠ ነው
ደሴ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ በምርጫው የድምጽ መስጫ እለት በህዝቡ ዘንድ የታየው የነቃ ተሳትፎ የመንግስት ስልጣን በምርጫ ብቻ መሆን እንዳለበት ትምህርት የሰጠ መሆኑን በደሴ ከተማ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የተካሄደ መሆኑን በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ተረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በተሟላ ዝግጅት ምርጫውን የመራበት፣ ያስተባበረበትና ያስፈፀመበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑም ተገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ከማለዳ እስከ ሌሊት ድምፃቸውን በመስጠት የነበራቸው ጠንካራ ተሳትፎ ለአፍሪካ የምርጫ ሂደት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን ታዛቢ ቡድኑ አመላክቷል።
አጠቃላይ የምርጫውን ሂደትና የህዝቡን ተሳትፎ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በደሴ ከተማና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮችን አነጋግሯል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የኢዜማ ደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና መረጃ ክፍል ኃላፊ ሻምበል ደምሌ ተረፈ፤ በድምፅ መስጫው እለት አጠቃላይ የህዝቡ ተሳትፎና ለመምረጥ የነበረው ትጋት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የምርጫው ሂደት በተረጋጋ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መካሄዱን አንስተው በህዝቡ ዘንድ የታየው የነቃ ተሳትፎም የመንግስት ስልጣን በምርጫ ብቻ መሆን እንዳለበት ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በአብን የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከድር ይመር፤ በበኩላቸው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የዜጎች የምርጫ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ግንባታ መሰረት እየያዘ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።
በህዝቡ ዘንድ የታየው ተሳትፎ ለፓርቲዎች ህዝብን በላቀ ቁርጠኝነት ለማገልገል ትልቅ አደራና ሃላፊነት የሰጠ እንደሆነም አንስተዋል።
በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ የደሴ ከተማ ተወካይ አሊ ሺበሺ፤ የምርጫው ሂደት የተረጋጋና ሰላማዊ እንደነበር አስታውሰው ዜጎች የነበራቸው ተሳትፎም አስደናቂ እንደነበር ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ አለማየሁ፤ በምርጫው ህዝቡ ላሳየው ጠንካራ ተሳትፎ አመስግነው ከዚህም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የህዝብን አደራ በከፍተኛ ሃላፊነት መወጣት እንዳለብን ተገንዝበናል ብለዋል።