ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ አካሂደዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ አካሂደዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄዳቸውን የአፍሪካ ሕብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች አስታወቁ።
የአፍሪካ ሕብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ሰባተኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታዛቢዎችን በማሰማራት ያደረጉትን ትዝብት አስመልክቶ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ እና የዑጋንዳ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንትና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ (ዶ/ር) በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኬኒያ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ዑሁሩ ኬኒያታ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጎልበት አስደናቂ ስራ ሰርቷል።
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት የኢትዮጵያን እና የዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በተከተለ መርህ በስኬት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።
ቴክኖሎጂን ጨምሮ በምርጫ ቅድመ ዝግጅትና ድምፅ አሰጣጥ ሂደት የተከናወኑ ተግባራትም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን በማሳለጥ በኩል ስኬታማ እንደነበር አስታውሰዋል።
የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙ ለመራጮች ተጨማሪ ዕድል በመስጠት ለአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ለተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች በድምፅ አሰጣጡ ሂደት ቅድሚያ መሰጠቱ የዜጎችን ተሳትፎ በእጅጉ ያረጋገጠ እንደነበር አስረድተዋል።
በመላው ኢትዮጵያ የምርጫ አስፈፃሚዎች እና የፀጥታ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በጥሩ ሁኔታ መወጣታቸውን፣ የመገናኛ ብዙኃንም በተመሳሳይ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ማከናወናቸውን አድንቀዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው ያሳየው ተሳትፎና ጀግንነት በእጅጉ የሚመሰገን መሆኑን አንስተዋል።
የዑጋንዳ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ (ዶ/ር)፤ የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አባላት በተገኙባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በታቀደለት ሰዓት ተጀምሯል ብለዋል።
የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ስምሪት በወሰዱባቸው የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማና ሶማሌ ክልሎችና ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተሞች በየጣቢያዎቹ በቂ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች ተሟልተው የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ግልጽነትና ለመራጮች እንቅስቃሴ እጅግ ምቹ እንደነበሩም አስታውቋል።
በምርጫው ዕለት በጣቢያዎች ረጃጅም ሰልፎች የነበሩ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ እስከ እኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ማራዘሙን ተከትሎ መራጩ ሕዝብ በከፍተኛ ትዕግሥትና እርጋታ ድምፁን መስጠት እንደቻለ ገልጸዋል።
የፀጥታ ኃይሎችም በየአካባቢው የተሰጣቸውን ሕዝባዊ አደራ በመወጣት ለምርጫው ሂደት ሰላማዊነት ከፍተኛ እና በጎ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል።
በምርጫው ሂደት የባለድርሻ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማና ሰላማዊ ምርጫ መሆኑን አረጋግጠዋል ብለዋል።