ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል
ወራቤ ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ዛሬ ሥራ አስጀምረዋል።
በማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከ6 የተለያዩ ተቋማት 20 አገልግሎቶች የሚሰጡ መሆናችውን ገልጸው በቀጣይ ይበልጥ እየሰፋ የሚሄድ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው እንዳሉት፡ መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመፍታት ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው።
በዞኑ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዞ መስጠት ስለመጀመሩም ጠቁመዋል።
ዛሬ በወራቤ ከተማ ተገንብቶ የተጠናቀቀው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቋት በመስጠት የማህበረሰቡን እንግልት ያስቀራል ብለዋል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል እንደገለፁት፤ መንግስት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
በወራቤ ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ለመቅረፍ በ260 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የዚሁ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማዋ ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል የገበያ ማዕከልም መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
የምርት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ዘመናዊ የግብይት ማዕከሉ የከተማዋን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት እንደሚያመጣ ተመላክቷል።
በመርሐ ግብሩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ፣ የክልሉና የስልጤ ዞን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።