የምርጫ ሂደቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ጠንካራ መሰረት እየያዘ መሆኑን ያመላከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ሂደቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ጠንካራ መሰረት እየያዘ መሆኑን ያመላከተ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጠንካራ መሰረት እየያዘ መሆኑን እንዳመላከተ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ አጠቃላይ የድምፅ አሰጣጡ ሰላማዊና የተረጋጋ ሆኖ ተጠናቋል።
የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ስርአትና የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ጠንካራ መሰረት እየያዘ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አበሻ ሺርኮ (ዶ/ር)፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ዜጎች ከማለዳ እስከ ሌሊት ያለድካምና መሰልቸት ድምፅ የሰጡበት መሆኑን አንስተዋል።
በምርጫው ሂደት የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ መታየቱ በተለይም ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን መሆን ፅኑ አቋም መኖሩን የሚያረጋግጥ ሆኗል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን የሚያዘው በዜጎች መልካም ፈቃድና ይሁንታ ብቻ መሆን እንዳለበት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ የምርጫ ሂደት መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም ዜጎች በምርጫ ሂደቱ ያሳዩትን ጠንካራ ተሳትፎ በሀገር ግንባታና የልማት ስራዎችም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጣሰው ታደሰ፤ በዘንድሮው ምርጫ በዜጎች የታየው ጠንካራ ተሳትፎ አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።
ለምርጫው ዜጎች ከማለዳ እስከ ሌሊት በመሰለፍ ጭለማ፣ ብርድና ፀሃይ ሳይበግራቸው ድምፃቸውን መስጠታቸው በሀገር ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዙን የሚያመላክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።