ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ዜጎች በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነቡበትን ዕድል እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዜጎች በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነቡበትን ዕድል እየፈጠረ መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በዜጎች መካከል ለዘመናት የዘለቁ መሰረታዊ የሃሳብ ልዩነቶችን በምክክር መፍትሔ በመስጠት ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ለዚህም በ2014 ዓ.ም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በአሁኑ ወቅት ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል አጀንዳ የማደራጀትና ግብዓት የማሰባሰብ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ የምክክር ሥርዓት መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል።

ኮሚሽኑ ያለፈባቸው ወሳኝ ምዕራፎችም በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ምክክር በማድረግ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ዜጎችም በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ብሔራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት የሚችሉበትን ስልጡን የጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክር ሂደቱም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ የተለያዩ አመለካከቶችና አጀንዳዎች በነፃነት የሚንሸራሸርበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በማደራጀት ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምክክር ጉዞ በዲጂታል አማራጭ በመሰነድ ቀጣዩ ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ የመሰነድ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምክክር ሂደት አሳታፊና አካታችነት በግልፅ እንደሚያሳይ ነው ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጨምረው የተናገሩት።

የምክክር ሂደቱን የመሰነድ ሥራ ጥናትና ምርምር ለማከናወንና ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ማጋራት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማደራጀት ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ በይፋ ለማስጀመር የመጨረሻ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ገልጸዋል።

በምክክር ሂደቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን ለውይይት በማቅረብ ብዝኅነትንና ሕብረ ብሔራዊነትን ታሳቢ አድርጎ የሚካሄድ መሆኑን አንስተዋል።

ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ አስፈላጊው የቴክኒክና የሎጀስቲክስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም