ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጤናማ ማህበረሰብን ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሸጋው ፈንታዬ ገለጹ።

ማህበሩ እነዚህን ስራዎች የሚደግፉ የምርምር፣ የአቅም ግንባታና ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ምቹ የአየር ፀባይ ሁኔታ እና ንጹህ አካባቢዎችን ለማስፋፋት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፣ በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄና ሌሎች መርሃ ግብሮች በተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙ ነው።


 

የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሸጋው ፈንታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጤናማ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ለዜጎች ተስማሚ የሆነ የመኖሪያ አካባቢን መፍጠር ይጠይቃል።

የደኖች ጭፍጨፋ እንዲሁም የአካባቢን ንጽህና አለመጠበቅ የዜጎች ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አንስተዋል።


 

በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንዲሁም የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ስራዎች የአካባቢ ጤናን በመጠበቅ ለማኅበረሰብ ጤና ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል። 

የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ዜጎችን ከተለያዩ በሽታዎች እንደሚጠብቅም አክለዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ስራዎች ላይ ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ማህበሩ እነዚህን ስራዎች የሚደግፉ የምርምር፣ የአቅም ግንባታና ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።


 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አለማየሁ ሀዲስ በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት እና የአካባቢ ንጽህናን አለመጠበቅ በዜጎች ጤና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን እና አካባቢን ንጹህ ለማድረግ የሚሰሩ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ምሁራን የአካባቢን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም