በዞኑ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በተከናወነ የንብ ማነብ ስራ ወደ 3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚጠጋ የማር ምርት ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በተከናወነ የንብ ማነብ ስራ ወደ 3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚጠጋ የማር ምርት ተገኘ
ደብረ ማርቆስ ፤ግንቦት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በተከናወነ የንብ ማነብ ስራ ወደ 3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚጠጋ የማር ምርት ማግኘት መቻሉን የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሃብት መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የንብና ሃር ልማት ባለሙያ አቶ ስማቸው ዳምጤ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በንብ ማነብ ስራ በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ በማነብ ስራ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በመደገፍና በማበረታታት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ማር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በዞኑ የሚገኙ ከ48 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ባሏቸው ከ200 ሺህ በላይ የንብ ቀፎዎች እስካሁን ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ማር ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
የተመረተውን ማር ለገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።
ምርቱም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ1 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው ለዚህም የተስተካከለ ዝናብ መኖር ለዕፅዋት ማበብ ምክንያት በመሆኑ ምርቱ ሊጨምር መቻሉን አስረድተዋል።
ይህም ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ በአማካኝ 30 ኪሎ ግራም፣ ከሽግግር ቀፎ 18 ኪሎ ግራምና ከባህላዊ ቀፎ ስምንት ኪሎ ግራም ማር እንዲገኝ በማስቻሉ የመጣ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል የአዋበል ወረዳ የእነቢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጌታሁን ይግዛው፤ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በንብ ማነብ ስራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ ሆኛለሁ ብለዋል።
በቅርብ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የለሙ አካባቢዎች ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸው ከ10 ዘመናዊና የሽግግር ቀፎዎች ከ190 ኪሎ ግራም በላይ ምርት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
የዚሁ ወረዳ የገሽ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ቢምረው አወቀ በበኩሉ ካሉት 13 ዘመናዊና የሽግግር የንብ ቀፎዎች ከ180 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጿል።