ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስኬት ተጠናቋል - ሜላትወርቅ ሃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስኬት ተጠናቋል - ሜላትወርቅ ሃይሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/ 2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ገለጹ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ሰባተኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ መጠናቀቅና ሂደት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በነቂስ ወጥተው ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድምፃቸውን ሲሰጡ መዋላቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ ረጃጅም ሰልፍ የነበረባቸውን የምርጫ ጣቢያዎች እስከ እኩለ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት እንዲቀጥል በማራዘም መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ወደኋላ በዘገየባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የነበሩ መራጮችን ረጃጅም ሰልፍ ማስተናገድ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፎ እንደተሰራበት አንስተዋል።
ትናንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደትም በስኬት መከናወኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የምርጫ ሂደቱን የሚከታተልና የሚቆጣጠር መፍትሔ ሰጪ ልዑክ በተለያዩ ክልሎች በማሰማራት ስኬታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ በአማራ ክልል፣ ሶማሌ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ የድምፅ ቆጠራ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለቅሬታዎች መፍትሔ ለመስጠትም በሕግ ክፍል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በስልክ ቁጥርና በምርጫ ታዛቢዎች በሚሰጥ ጥቆማ ከስር ከስር በማጣራትና በማረጋገጥ የእርምት እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የድምፅ ቆጠራ ያጠናቀቁ ምርጫ ጣቢያዎች የተሰጠውን ድምፅ በመለጠፍ በአደባባይ ለህዝብ ይፋ እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም በእያንዳንዱ ምርጫ ክልል የተሰጠውን የድምፅ ውጤት በመደመርና በዝርዝር በመመልከት አጠቃላይ ድምር ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን አስረድተዋል።