የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላላ ምርጫው ያሳዩትን ተሳትፎ በማስቀጠል ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላላ ምርጫው ያሳዩትን ተሳትፎ በማስቀጠል ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገለጹ
ሻሸመኔ ፤ግንቦት 25/2018 (ኢዜአ)፦በጠቅላላ ምርጫው ያሳዩትን ተሳትፎ በማስቀጠል ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የምዕራብ አርሲ ዞን የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ሂደቱን አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በህዝብ ድምጽ አሸናፊ ሆኖ ከሚመሰረተው መንግስት ጋር በመሆን ልማትን ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በምርጫው የታየው የሕዝብ ንቁ ተሳትፎን በማጎልበት ልማትን ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የምዕራብ አርሲ ዞን አባ ገዳዎች ሰብሳቢ አባ ገዳ ነጌሶ ገመቹ፤ በጠቅላላ ምርጫው የታየውን የህዝቡን ጠንካራ ተሳትፎ በማስቀጠል ዴሞክራሲን ለማጎልበትና ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ቀበኔ ደሶ፤ በጠቅላላ ምርጫው ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰለጠነ ፖለቲካ ያለውን ዝግጁነትና መንግስት በህዝብ ይሁንታ ብቻ መመስረት እንዳለበት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መሠረት ገብረማርያም በበኩላቸው፤ በድምጽ መስጠት ወቅት ያሳየነውን ንቁ ተሳትፎ ቀጣይ ልማትን በማፋጠን እንደግመዋለን ብለዋል።