ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ልምምድ የታየበት ነው - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ልምምድ የታየበት ነው - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት የተሻለ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ልምምድ የታየበት መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ትናንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ውሎ፤ የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎችም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ ተካሂዶ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።
በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን እየለጠፉ ሲሆን፤ ዜጎችም ጊዜያዊ ውጤቶችን እየተመለከቱ ይገኛል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ታደሰ መኮንን እንደገለጹት፤ በምርጫው ይሆነኛል፤ ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ በነፃነት ድምፅ ሰጥተዋል።
በምርጫ ሂደት የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህዝብ ከፍተኛ ተሳትፎም የዴሞክራሲ ባህልን በማጎልበት ለትውልድ መሰረት ጥሎ እንዳለፈ አንስተዋል።
ሌላኛው የ89 አመት የዕድሜ ባለጸጋ ኪሮስ ገብሩ በሰጡት አስተያየት፤ ቀሪ የዕድሜ ዘመናቸውንና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ለማድረግ ይሰራል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
የምርጫው በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁ ቀጣዩ ትውልድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልምምድ የበለጠ የሚያጎለብትበት መሰረት እንደጣለ ተናግረዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበረው ከፍተኛ ተሳትፎ በድምፃችን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ካለን ፅኑ ፍላጎት የሚመነጭ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አማረች ፀጋዬ ናቸው።
በምርጫውም ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ወደተሻለ ምዕራፍ ያሻግራል ለሚሉት ድምፅ በመስጠት ለሀገራቸው መምረጣቸውን ገልጸዋል።
በምርጫ ሂደት በሚፎካከሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ማሸነፍና መሸነፍ ተፈጥሯዊ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ዕድገት ሰላምና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።