የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን ዕድገትና አንድነት የምናስቀጥልበትን ቃልኪዳን ያኖርንበት ታሪካዊ ሁነት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን ዕድገትና አንድነት የምናስቀጥልበትን ቃልኪዳን ያኖርንበት ታሪካዊ ሁነት ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን ዕድገትና አንድነት የሚያስቀጥሉበትን ቃልኪዳን ያኖሩበት ታሪካዊ ሁነት መሆኑን በሶማሌ ክልል የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ትናንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ውሎ፤ የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎችም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ ተካሂዶ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።
ይህን ተከትሎም በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን እየለጠፉ ሲሆን፤ ዜጎችም ጊዜያዊ ውጤቶችን እየተመለከቱ ይገኛል።
በሶማሌ ክልል የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎችም በ38 የምርጫ ጣቢያዎች ይወክሉናል ለሚሏቸው የክልልና የሕዝብ ተወካዮች ዕጩ ተወዳዳሪዎች በነፃነት ድምፅ በመስጠት መርጠዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደገሀቡር ከተማ ነዋሪዎች፤ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትጋት ይሰራሉ ለሚሏቸው ዕጩዎች ይሁንታን የሚሰጥ ምርጫ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አሕመድ ረሺድ፤ በዘንድሮው ምርጫ ሂደት ያለ አንዳች እንከን ይበጀናል ለምንለው ዕጩ ድምፅ በመስጠት የመረጥንበትና ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብታችንን በነፃነት የተጠቀምንበት ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ምርጫ ያለ ማንም ተፅዕኖ ይበጀናል የሚሉትን ወኪል መምረጣቸውም ሂደቱን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ምርጫ ከሚመረጠው መንግሥት ጋር ለሀገራችን ዕድገትና አንድነት የምንሰራበትን ቃልኪዳን ያኖርንበት ነው ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አብዲወሊ ሙሴ በበኩላቸው፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመምረጥ መመረጥ ሕገ-መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በተግባር ተጠቅመናል ብለዋል።
በምርጫ ሂደቱም ለህዝብ ተጠቃሚነት ይበጃል ለሚሉት ዕጩ ያለ አንዳች ጎትጓች ድምፅ በመስጠት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መምረጣቸውን ገልጸዋል።
ምርጫው ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱም ኢትዮጵያዊያን ለሀገር ዕድገትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለንን ጥንካሬ ለዓለም የገለጠ የዜግነት ድምፅ ነው ብለዋል።
በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ወኪሌን በነፃነት መርጫለሁ ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ሀሰን ኢብራሂም ናቸው።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት በመጣል የሀገር አንድነት ያረጋገጠ ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ተናግረዋል፡፡