ቀጥታ፡

በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ 

አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2018 (ኢዜአ)፦በግብርና እና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ፡፡    

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማት፣ በሥራ ፈጠራ ማበረታቻ እና በፋይናንስ አቅርቦት ዙሪያ ያላቸውን የጋራ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። 

ስምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ካሳ (ዶ/ር) ፈርመውታል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት፤ የወጣቶችን ፍላጎት የተገነዘበ አገር የለውጥ ጉዞው የተቃና ይሆናል።  

የኢትዮጵን ሁለንተናዊ እድገትና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የወጣቱን እምቅ አቅምና የፈጠራ ሐሳቦች ማዕከል ያደረጉ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተቋማት በቅንጅት መሥራት ጠንካራ አገር ከመገንባት አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል።

የሁለቱ ተቋማት ስምምነትም ለወጣቶችና ለሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አቅርቦትን በዘላቂነት በማቅርብ፣ የነገ ተስፋቸውን ለማለምለም ምቹ ምኅዳር የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በተለይም የወጣቶችን በክህሎት የታገዙ የፈጠራ ሐሳቦች በፍጥነት ወደ ተግባርና ወደ አምራችነት እንዲቀየሩ ትልቅ ድልድይ እንደሚሆን ተናግረዋል።


 

በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወጣቶች አነስተኛ መጠን ያለው ብድር እና የግብዓት አቅርቦት መስጠትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በተለያዩ ክልሎች በግብርና ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ ወጣቶች የገንዘብና የግብዓት አቅርቦት ማድረግን ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ የፋይናንስ ተቋማቱ ቀደም ሲል ያቀርቡበት ከነበረው የወለድ መጠን ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም