ፌዴራል ፖሊስ የታጠቃቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የምርጫ ሂደቱን ውጤታማነት በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ፖሊስ የታጠቃቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የምርጫ ሂደቱን ውጤታማነት በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የታጠቃቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰባተኛው ጠቅላላ የምርጫ ሂደትን ውጤታማነት በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ ሚና መጫወቱ ተገለጸ።
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ትናንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ውሎ፤ የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎችም እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ ተካሂዶ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።
ይህን ተከትሎም በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን እየለጠፉ ሲሆን፤ ዜጎችም ጊዜያዊ ውጤቶችን እየተመለከቱ ይገኛል።
ይህ የድምጽ አሰጣጥ ሂደትም ፍጹም ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ እና ገለልተኝነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፍያ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በምርጫው ወቅት ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን የሚሰጡበትን ሂደት ለማገዝ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።
በተለይም በአዳዲስና ፈጣን እድገት ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ከነባሮቹ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማቶች ጋር በማቀናጀት፣ የፖሊስ ሰራዊት ስምሪት እና የምርጫ ጣቢያዎችን እንቅስቃሴ እያንዳንዱን በቀጥታ ለመከታተል መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም በየአካባቢው የሚታየውን የፀጥታ ሁኔታና የምርጫ ድባብ አመራሩ ከኮማንድ ኮንትሮል ማዕከል ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሁሉም የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በሰራው ስራ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡