የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትና ድምጽ አሰጣጥ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትና ድምጽ አሰጣጥ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት ነው
ሆሳዕና ፤ግንቦት 25/2018 (ኢዜአ)፦የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትና ድምጽ አሰጣጥ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለፀ።
ምክር ቤቱ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ ደምስ ገብሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መወዳደራቸውን ተናግረዋል።
ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ መጠናከር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አጠቃላይ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ከቅድመ ምርጫ እስከ ድምጽ መስጫው እለት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸውን አማራጭ ሀሳቦች ለህዝብ በነጻነት በማቅረብና ተገቢ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣታቸውንም አስታውሰዋል።
ህዝቡ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ድምጹን ለመስጠት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጠናከር ያለውን ፍላጎት በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በክልሉ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንደተካሄደና ዜጎችም በንቃት የተሳተፉበት መሆኑንም አቶ ደምስ አስታውቀዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢና የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ አቶ በረከት ከድር በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ታይቷል ብለዋል።
ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም ዜጎች በጠቅላላ ምርጫው ሂደትና በድምጽ አሰጣጡ ጠንካራ ተሳትፎ ማድርጋቸውን ተናግረዋል፡፡