ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጋው ወራት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በርካታ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል

ጊምቢ፤ ግንቦት 25 /2018  (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጋው ወራት በበጎ ፈቃደኞች በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶች፣ በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት የበጋ ወራት በ20 የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ዘርፎች በተሰማሩ ፈቃደኞች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የአዳዲስ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና የነባር ቤቶች እድሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የደም ልገሳ እና ሌሎች የአካባቢ ልማት ሥራዎች ይገኙበታል ነው ያሉት።

በዚህም በአቅም ማነስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የበርካታ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት መቻሉን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ስራው በቀጣዩ የክረምት ወራትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለዚህም ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

በበጋ ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሳተፉ ዜጎች መካከል ወጣት ለሊሳ አብዲ በበጎ ፈቃድ ተግባር ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ የህሊና እርካታን ይሰጣል ብሏል።

በበጋው የታየውን መነሳሳት በመቀጠል፣ በክረምቱም የወገኖቻችንን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ሲል ገልጿል።

ሌላዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ኩላኒ ጫቃ በአቅም ማነስ ምክንያት ቤቴን ማደስ ባለመቻሌ፣ ለዓመታት በበጋ ፀሐይ እንዲሁም በክረምት ብርድና ዝናብ ስቸገር ኖሬያለሁ ይላሉ።

ዘንድሮ በበጎ ፈቃደኞች ቤቴ ታድሶልኝ ችግሬ ተቃሏል ያሉት ወይዘሮዋ በተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፣ ለተባበሩዋቸው አካላትና ለወጣቶቹ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም