ቀጥታ፡

በምርጫው ላይ ያሳየነውን ጠንካራ ተሳትፎ በቀጣይ በጋራ ሀገር ለመገንባት ማዋል አለብን- የጅማ ከተማ ነዋሪዎች

ጅማ ፤ግንቦት 25/2018(ኢዜአ)፡- በምርጫው ላይ ያሳየነውን ጠንካራ ተሳትፎ በቀጣይ በጋራ ሀገር ለመገንባት ማዋል አለብን ሲሉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በጅማ ከተማ ቆጠራ በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶች እየተለጠፉ ሲሆን፣ ሕዝቡም እየተመለከተ ይገኛል።

በጅማ ከተማ ባሉት 117 የምርጫ ጣቢያዎች ነዋሪዎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፃቸውን ሲሰጡ መዋላቸውን የጅማ ከተማ የምርጫ ክልል መግለጹ ይታወቃል።

በከተማዋ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ሲመለከቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፤ አጠቃላይ በምርጫ ሂደቱ በትናንትናው እለት ደግሞ ድምፅ ለመስጠት ከማለዳ እስከ ምሽት የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በምርጫው ላይ ያሳየነውን ጠንካራ ተሳትፎ በቀጣይ በጋራ ሀገር ለመገንባት ማዋል አለብን ሲሉ አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።

ትላንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምጻቸውን ሰጥተው፣ በማለዳ ውጤት ለማየት በምርጫ ጣቢያ የተገኙት አቶ አወል አብዱረህማን፤ ሀገርን መውደድ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ በምርጫ መሳተፍ ነው ይላሉ።

ሰላማዊ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቁ የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ በምርጫ ያሳየነውን ተሳትፎ በሌሎች የልማት ሥራዎችም መድገም አለብን ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የምርጫ ውጤትን በፀጋ በመቀበል የዴሞክራሲ መሠረትን ማፅናትና የሀገርን ልማት ማፋጠን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በሽር አህመድ በበኩላቸው፣ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ አድርገው መምረጣቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ሀገር በምትፈልገው መስክ ሁሉ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ መሳተፋቸውን ያስታወሱት አቶ በሽር፤ ይህ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ ዜጎች የተሳተፉበትና ሰላማዊ መሆኑ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም በምርጫው የተሳተፉ አካላት ሁሉ ውጤቱን አምኖ በመቀበል የኢትዮጵያን ዕድገትና ሰላም ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በምርጫው ድምጿን በመስጠቷ ትልቅ ደስታ እንደተሰማት የገለጸችው ወይዘሮ ዘቢባ ጀማል በበኩሏ፣ ውጤቱን ለማየት በማለዳው በጊንጅ ጉድሩ ቀበሌ ገጠር ቴክኖሎጂ ምርጫ ጣቢያ መገኘቷን ተናግራለች።

በቀጣይም በምርጫው ላይ ያደረጉትን ተሳትፎ ሀገር በምትፈልገው የልማት ሥራዎች ላይ ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጅማ ከተማ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው በጊንጅ ጉድሩ ቀበሌ ገጠር ቴክኖሎጂ ምርጫ ጣቢያ፣ በውኃ ፍሳሽ ምርጫ ጣቢያ እና በሌሎችም ጣቢያዎች የምርጫ ውጤቶች በአሁኑ ሰዓት እየተለጠፉ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም