ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ስራ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ስራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2018(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን መልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ስራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማግስት፣ዛሬ ጠዋት ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ስራ አስጀምረናል ብለዋል።
ይህ ትልቅ ተነሳሽነት፤የተራቆቱ አካባቢዎችን በዘመናዊ የአፈር ጥበቃ እና በወንዝ ማጣራት ወደ አረንጓዴ ስፍራዎች በመቀየር፣ የፍራፍሬ ፓርኮችን ከእግር ጉዞ እና ከብስክሌት መንገዶች ጋር በማቀናጀት መዲናችንን አድሷል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 22.25 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማትን የሚሸፍን መሆኑን ገልጸው፥ይህ የማይቆራረጥ የልማት ስራችን ህያው ምስክር ከመሆኑም በላይ የሃገራዊ ዕድገታችን፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የከተማ እድሳት በተግባር የታየበት ነው ብለዋል።