ቀጥታ፡

የድምጽ መስጫ ሰዓት መራዘሙ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም አስችሎናል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦የድምጽ መስጫ ሰዓት መራዘሙ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም እንዳስቻላቸው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ የተራዘመ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

በዚህም ምርጫ ቦርድ በሰጠው መመሪያ መሰረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 19 እና 20  በምርጫ ጣቢያዎች  ዜጎች ድምፃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ 

በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ምርጫ ጣቢያ ድምፅ ሲሰጡ ያገኘናቸው እየሩሳሌም ይስሀቅ ምርጫ ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን መብት የሚጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምርጫው እስከ እኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት መራዘሙ የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አሸናፊ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው በምሽት ይወክለኛል የሚለቱን ፓርቲ መምረጥ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ቦርዱ ባራዘመው ሰዓት ድምጽ ያልሰጡ ዜጎች ድምጻቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ 

  የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ካላቸው ተነሳሽነት አኳያ ምሽቱ ሳይገድባቸው ለመምረጥ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ እልፍነሽ ክፍሌ ናቸው፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም