ቀጥታ፡

የምርጫው ሰአት በመራዘሙ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን ይሆነናል የምንለውን አካል እንድንመርጥ እድል ፈጥሮልናል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 24/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሰአቱን በማራዘሙ ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን ይሆነናል የምንለውን አካል እንድንመርጥ እድል ፈጥሮልናል ሲሉ መራጮች ገለፁ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዛሬው እለት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እየሰጡ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የድምፅ መስጫ ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እስከ ዕኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ድረስ የተራዘመ መሆኑን አስታውቋል።

ኢዜአ በመዲናዋ ተዘዋውሮ የተለያዩ ምርጫ ክልል ስር የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች እንደተመለከተው ዜጎች በረዣዥም ሰልፎች ተሰልፈው እየመረጡ ይገኛሉ።

በዚሁ ወቅት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ መራጮች እንዳሉት የምርጫ ሂደቱ መራዘም ለኛ ሁለተኛ እድል እንደመስጠት ነው።

አስተያየት ሰጪዎቹ ለመምረጥ ቀደም ብለው የመጡ ቢሆንም ሰልፎቹ ረጃጅም ስለነበሩ የምርጫ ሂደቱ የሚያበቃበት ስዓት ሲደርስ ተስፋ ቆርጠው እንደነበረ ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ የምርጫ ሂደቱን በማራዘሙ እኛ ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታችን ተጠቅመን ይሆነናል የምንለውን አካል እንድንመርጥ እድል ሰጥቶናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም