ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በሚያጠናክር መልኩ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በሚያጠናክር መልኩ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 24/2018 (ኢዜአ)፦ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ባህልን በሚያጠናክር መልኩ እየተካሄደ መሆኑን በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዛሬ ማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና የሕብረት ለዴሞክራሲና ለነፃነት ፓርቲዎችም እየተፎካከሩ ይገኛል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሕመድ ያሲን እና የሕብረት ለዴሞክራሲና ለነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር መሐመድ አድን በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በምርጫ ከተወዳደረ ከዓመታት በኋላ በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አሕመድ ያሲን፤ በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ በሰጡበት ዳኖድ ወረዳ ምርጫው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፓርቲው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከዓመታት በኋላ በነፃነት ለመወዳደር ያስቻላቸው ወሳኝ ዕድል እንደተፈጠረ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው አስደናቂ የትብብር መንፈስ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ልምምድን ማጠናከር የሚስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ኦብነግ ከዓመታት በኋላ በዚህ የምርጫ ፉክክር መሳተፉ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የለውጥ ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሕብረት ለዴሞክራሲና ለነፃነት ፓርቲ ሊቀ መንበር መሐመድ አድን በበኩላቸው፤ የእስካሁኑ የምርጫ ሂደት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በሚያጠናክር መልኩ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
እርሳቸውም በሶማሌ ክልል ደምበል ወረዳ ድምፅ መስጠታቸውን በመጠቆም፤ በምርጫ ሂደቱም ዜጎች በነፃነት ድምፅ እየሰጡ ነው ብለዋል።
መራጮችም በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚገኘውን ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ የመራጭነት መብት በመጠቀም በነቂስ ወጥቶ ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምፁን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።