የሲቪል ማኅበራት ገለልተኛ ትዝብት የምርጫውን ተዓማኒነትና ስኬት ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማኅበራት ገለልተኛ ትዝብት የምርጫውን ተዓማኒነትና ስኬት ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታንና የተቋማትን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ አገር በቀል የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች እያበረከቱት ያለው ወሳኝ ሚና በተግባር እየታየ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ያወጣው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የእኩለ ቀን የትዝብት ሪፖርት፣ ማኅበራቱ ለምርጫው ግልጽነትና ስኬት የቆሙ ታማኝ የሕዝብ ዓይን መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጧል።
ኅብረቱ ከ3,100 በላይ ፕሮፌሽናል አገር በቀል ታዛቢዎችን በመላ አገሪቱ በጥናት ላይ በተመሠረተ ተመጣጣኝ (Proportional) ስልት በማሰማራት፣ በዜጎች ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ የምርጫ ትዝብት (Citizen Election Observation) በላቀ ብቃት ማከናወን ችሏል።
ይህ የሲቪክ ማኅበራት ግዙፍ ስምሪት በምርጫ ሂደቱ ላይ የላቀ አመኔታን የፈጠረ ሲሆን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ከፍተኛ ድርጅታዊ ብቃትና ሕጋዊ ተገዢነት በገለልተኝነት ለመገምገም አስችሏል።
በሲቪል ማኅበራቱ የትዝብት ውጤት መሠረት፣ የምርጫ ሂደቱን ግልጽና ተዓማኒ ከማድረግ አንጻር ምርጫ ቦርድ አበረታች ሥራዎችን አከናውኗል።
ማኅበራቱ ባሰማሯቸው ታዛቢዎች አማካኝነት ባደረጉት ክትትል፣ 99% በሚሆኑት ጣቢያዎች ላይ ታዛቢዎች ያለምንም ገደብና እንቅፋት ገብተው ሂደቱን በነፃነት እንዲታዘቡ ተፈቅዶላቸዋል።
ይህም በተቋማቱና በሲቪክ ማኅበራቱ መካከል ያለውን መልካም አጋርነት ያሳያል።
የቁሳቁስ ስርጭትና የሰው ኃይል ዝግጁነትን በተመለከተም ማኅበራቱ ባደረጉት ሳይንሳዊ ምልከታ፣ 97% በሚሆኑት ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት በፊት በቦታቸው ተገኝተው ጣቢያዎችን በወቅቱ መክፈታቸውንና 95% በሚሆኑት ጣቢያዎች ደግሞ ከሦስት በላይ አስፈጻሚዎች በሥራ ገበታቸው ላይ መገኘታቸውን በሪፖርታቸው አረጋግጠዋል።
የሲቪል ማኅበራቱ ሪፖርት የምርጫውን አካታችነት በግልጽ ያሳየ ነው። ከተመዘገቡት ጣቢያዎች መካከል 61% የሚሆኑት ከአንድ በላይ ሴት አስፈጻሚዎች የነበሯቸው ሲሆን፣ 26% የሚሆኑትን ጣቢያዎች በበላይነት የመሩት ሴቶች መሆናቸውንና 13% በሚሆኑት ጣቢያዎች ላይ ደግሞ አካል ጉዳተኞች በአስፈጻሚነትና በጣቢያ ኃላፊነት መመደባቸውን ታዛቢዎቹ በምስክርነት መዝግበዋል።
በተጨማሪም 97% ጣቢያዎች በሕግ በተፈቀዱ ገለልተኛ ሥፍራዎች መቋቋማቸውንና 96% በሚሆኑት ጣቢያዎች ክልል ውስጥ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ አለመኖሩን የሲቪክ ማኅበራቱ ታዛቢዎች አረጋግጠዋል።
ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የተደረገውን ምቾት በሚመለከትም፣ 96% ጣቢያዎች ለሴቶችና አረጋውያን፣ እንዲሁም 93% ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞች ያለ ረዳት ገብተው ድምፅ እንዲሰጡ ተደርገው መዘጋጀታቸውንና የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ መሟላታቸውን ማኅበራቱ አሳይተዋል።
በአጠቃላይ ኅብረቱ ያቀረበው የእኩለ ቀን ሪፖርት፣ አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ስኬታማ፣ ሕጋዊና አካታች እንደነበሩ ያረጋገጠ ነው።
ይህ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ሚና፣ በኢትዮጵያ ተዓማኒና ብቁ የምርጫ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ብሔራዊ ጉዞ ውስጥ ተቋማዊ ግልጽነትንና የሕዝብ አመኔታን ለማስፈን ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ በተግባር ያሳየ ሆኗል።