ቀጥታ፡

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ነጻና ዴሞክራሲያዊ ነው-ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ጋምቤላ፤ግንቦት 24/2018 (ኢዜአ)፦የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ነጻና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በጋምቤላ ክልል የተወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ባለፉት ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች ነጻ፣ አሳታፊና የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት በተግባር ጎልቶ የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሕዳሴ ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ አስተባባሪ መምህር ሻምበል ቶላ እንዳሉት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ተናግረዋል።

መራጩ ህዝብም ከማለዳው ጀምሮ በነቂስ ወጥቶ ያለማንም ተጽዕኖ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ይበጀኛል ላለው ፓርቲ ድምጹን በነፃነት የሰጠበት ምርጫ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች ፍጹም ዴሞክራሲያዊ መብትና ተሳትፎ ጎልቶ የታየበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋትቤል ቦል ናቸው።

በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ህዝቡ ያለማንም ተጽዕኖ ይመራኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት ሲሰጥ መዋሉንም ተናግረዋል።

ምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መካሄዱን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፔን ኡጁሉ ናቸው።

የዘንድሮው ምርጫ የፖለቲካ ምህዳሩ ይበልጥ የሰፋበትና ህዝቡም በነቂስ ወጥቶ የተሳተፈበት መሆኑን አቶ ፔን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም