ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ያረጋግጣል ብለን ያመነውን አካል መርጠናል - መራጮች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ያረጋግጣል ብለው ያመኑበትን አካል መምረጣቸውን ኢዜአ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ያናገራቸው መራጮች ገለፁ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዛሬው እለት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እየሰጡ ነው።

ኢዜአ በአራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 2 ፣ 14  እና 16 ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ድምፃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠቅላይ ቤተክህነት ስብከተ ወንጌል መልአከ ሃይል አፈወርቅ ዮሃንስ ምርጫ የኢትዮጵያ የወደፊት እጣፈንታ የሚወሰንበት በመሆኑ በጠዋት በምርጫ ጣቢያ በመገኘት ለሀገር ይበጃል የሚሉትን አካል መምረጣቸውን ተናግረዋል።

ምርጫው የተረጋጋ ፍትሐዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ህዝቡም ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚለውን አካል ሊመርጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ምዑዝ ገብረህይወት በበኩላቸው፤ ምርጫ የዲሞክራሲ ሂደት ማረጋገጫ መሆኑ በመረዳት ከጠዋቱ 11 ሰዓት ላይ መጥተው ይሆነኛል የሚሉትን ያለምንም ተፅእኖ መርጫለሁ ብለዋል።

አስተያየት ሰጪው ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው ያሉ ሲሆን ካርድ የወሰዱ ሰዎችም ይሆነኛል ይበጀኛል የሚሉት አካል እንዲመርጡ ምክረዋል።

የሺ ግርማና እና ጥሩወርቅ አስፋው በበኩላቸው ምርጫ ለአንድ ሀገር ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት የአካል ጉዳታቸው ሳይገድባቸው በጠዋት በመምጣት ለኢትዮጵያ የተሻለ ይሰራል ብላ ያመነችውን ፓርቲ መምረጥዋን ነው የገለፀችው።

አስተያየት ሰጪዎቹ የአካል ጉዳት ላለባቸውና አቅም ደካሞች ቅድሚያ መሰጠቱ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ሌላውም ነዋሪ የአንድ ሰው ድምፅ ዋጋ እንዳለው በመረዳት ሊመር እንደሚገባ ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም