ቀጥታ፡

የጠቅላላ ምርጫው የእስካሁኑ ሂደት ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የዜጎች የነቃ ተሳትፎ የታየበት ነው - ተፎካካሪ ፓርቲዎች

አዳማ፤ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፡-ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የእስካሁኑ ሂደት ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የዜጎች የነቃ ተሳትፎ የታየበት ነው ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲን (ኢብአፓ) ወክለው በአዳማ አንድ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡት እጩ ተወዳዳሪ ፓስተር በየነ ደሳለኝ በሰጡት አስተያየት፤ ካለፉት ዘመናት አንጻር በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው ይህንን ዕድል በመጠቀም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተወዳደረ መሆኑን ጠቁመው፤ ሂደቱም ነጻ፣ ፍትሃዊ እና አካታች መሆኑን ተናግረዋል። 

ሕዝቡ በምርጫው እያሳየ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት ፓስተር በየነ፤ ፓርቲያቸው የምርጫን ውጤት በጸጋ ለመቀበል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማንም ቢያሸነፍ ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀታቸውንና ፓርቲያቸው ከተሸነፈም ለቀጣይ ጊዜ ራሱን እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።


 

በሌላ በኩል በአዳማ ምርጫ ክልል ሁለት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የሚወዳደሩት አቶ ሀብታሙ ተሰማ፤ ሕዝቡ ያለምንም ቀስቃሽ በማለዳ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን እየሰጠ መሆኑን አድንቀዋል። 

ይህም በሀገሪቱ መንግሥት የሚመሰረተው በሕዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን በግልጽ ያሳያል ብለዋል።

የዘንድሮውን ምርጫ ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ለመራጩ ሕዝብ ቀላልና ግልጽ መሆኑ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በዘንድሮ ምርጫ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ መልካም ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው ይህንን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በአግባቡ በመጠቀም በምርጫው ተፎካካሪ ሆኖ እየተወዳደረ መሆኑንም አክለዋል።

አቶ ሀብታሙ አክለውም ድምፅ ከተሰጠ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ የሚያደርገውን የምርጫ ውጤት በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም