የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ ስላለው ሁሉም ድምፁን ሊሰጥ ይገባል - የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ - ኢዜአ አማርኛ
የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ ስላለው ሁሉም ድምፁን ሊሰጥ ይገባል - የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦ የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ ስላለው እስካሁን ያልመረጡት ወጥተው ድምፃቸውን ሊሰጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ገለጸ።
በጎንደር ከተማ ምርጫ ክልል አንድ የኢዜማ የተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ ዝናህወርቅ ታደለ በሚወዳደሩበት የጎንደር ከተማ ምርጫ ጣቢያ አንድ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
በጎንደር ከተማ በሚገኙ ሁለት የምርጫ ክልሎችና 240 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ እየሰጡ ነው።
ግንቦት 24ን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በዛሬው እለት ከጠዋቱ ከ12 ሰዓት ጀምረው በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ይበጀኛል የሚለውን በመምረጥ ላይ ይገኛል።
በጎንደር ከተማ ምርጫ ክልል አንድ የኢዜማ የተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ ዝናህወርቅ ታደለ እንዳሉት፤ መራጩ ህዝብ ወጥቶ ምርጫ እያካሄደ ነው።
የሀገር ዴሞክራሲ የሚገነባበት መንገድ አንዱ ምርጫ መሆኑን በመጥቀስ፤ መራጩ ህዝብ እስከመጨረሻው ድረስ እንዲመርጥም ጠይቀዋል።
ዴሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚገነባ አይደለም ያሉት አቶ ዝናህወርቅ፤ ለዳበረ ዴሞክራሲ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝነት አለው ብለዋል።