ቀጥታ፡

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ጎንደር፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን በጎንደር ከተማ በምርጫው የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

በጎንደር ከተማ በምርጫ ክልል አንድ ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) ሊቀመንበር አውግቸው ማለደ እንደገለጹት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የታየበት ነው፡፡

ፓርቲው በሚወዳደርባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ወኪሎቹን መድቦ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ያለማንም ተጽእኖ እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለአንድ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን ፓርቲው ያጋጠመው ችግር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በምርጫ ክልል አንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እጩ ተወዳዳሪ ዝናወርቅ ታደለ በበኩላቸው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው ብለዋል፡፡

የቅድመ ምርጫው ሂደት ዴሞክራሲያዊ እንደነበር አንስተው ዛሬ እየተካሄደ ባለው የድምጽ አሰጣጥ ሂደትም መራጩ ህዝብ ነጻ በሆነ መንገድ ድምጹን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም