ቀጥታ፡

በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ነጋችንን በመወሰን ለሚበጀን ፓርቲ ድምፅ ሰጥተናል - በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ምርጫ ክልል መራጮች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ነጋችንን በመወሰን ለሚበጀን ድምፅ ሰጥተናል ሲሉ በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ምርጫ ክልል መራጭ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን መራጮችም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምረው ድምፃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ምርጫ ክልል መራጮች እንዳሉት፤ ምርጫ ዜጎች የሚያስተዳድራቸውን መንግስት የሚመሰርቱበትና ነጋቸውን የሚወስኑበት ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ፤ ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ በማለዳ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት ድምፃቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኛ መሆኔ መብቴን ከመጠቀም አያግደኝም ያሉት መራጭ ዳንኤል ሙክታር በበኩላቸው ምርጫ የሚመራንን መንግስት በራስ መወሰን የሚያስችል በመሆኑ አካል ጉዳተኞች በምርጫው በነቂስ ወጥተው በመምረጥ ነጋቸውን ዛሬ እንዲወስኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አንተነህ እውነቱ ይጠቅመኛል ላሉት ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት የምርጫውን ዕለት በጉጉት ሲጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል።

ምርጫው ለልጆቻችን የተሻለ ሀገር ማስረከብ የሚያስችል በመሆኑ ህብረተሰቡ በቀሪ ሰዓት ድምፁን በመስጠት የሚበጀውን ሊመርጥ እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ ሀና መኮንን እና እናትነሽ አሸብር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም