ቀጥታ፡

ለማየት ባልታደልም በልጄ እየተመራሁ መጥቼ ድምፄን ሰጥቻለሁ - የ70 ዓመቱ አዛውንት

ሆሳዕና፤ ግንቦት 24/2018(ኢዜአ)፦ ለማየት ባልታደልም በልጄ እየተመራሁ መጥቼ ድምፄን ሰጥቻለሁ ሲሉ በሆሳዕና ከተማ የሚኖሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት ተናገሩ።

በሆሳዕና ከተማ ጀሎ ናረሞ ቀበሌ የሚኖሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት ዘኪዎስ መሎሮ ማየት ስለተሳናቸው የሚንቀሳቀሱት በእገዛ ነው።

የዛሬው ፕሮግራማቸው በጉጉት የጠበቁት፣ ለሀገርና ለዜጎች ሊሰራ ይችላል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ በመሆኑ ቀደም ብለው ተገኝተዋል።

ለምርጫው ልጃቸው እየመራ እንዲወስዳቸው እና ድምጻቸውን እንዲሰጡ በመወሰን በሆሳእና ከተማ ካርድ ወደ ወሰዱበት ምርጫ ጣቢያ ማልደው በመገኘት ድምፃቸውን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሁላችንም ኩራታችንና የልጆቻችን የወደፊት ህልም የሚሰራባት የጋራ ቤታችን ነች ያሉት አቶ ዘኪዎስ ሀገራችንን የምንወድ ሁሉ መሪዎቿን መምረጥ የግድ ይለናል ብለዋል።

እኔም ለማየት ባልታደልም በልጄ እየተመራሁ መጥቼ ድምፄን ሰጥቻለሁ፤ በዚህም ተደስቻለሁ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም