ቀጥታ፡

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በርካታ ጨዋታዎችን በማድረግ ክብረ ወሰን የያዘው ጀምስ ሚልነር ራሱን ከእግር ኳስ ተጫዋችነት አገለለ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24 /2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ የምንጊዜም ከፍተኛውን የጨዋታ ተሳትፎ ክብረ ወሰን የያዘው ጀምስ ሚልነር፣ ከ24 ዓመታት የሊግ ቆይታ በኋላ በ40 ዓመቱ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በረጅም የእግር ኳስ ዘመኑ ለሊድስ ዩናይትድ፣ ኒውካስል ዩናይትድ፣ አስቶንቪላ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን ተጫውቷል።

ያለፉትን ሶስት የውድድር ዓመታት በብራይተን ያሳለፈው ሚልነር፣ የእግር ኳስ ዘመኑን የጀመረው በልጅነት ክለቡ ሊድስ ዩናይትድ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2002 ገና በ16 ዓመቱ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረጉ ይታወሳል።

ተጫዋቹ በአጠቃላይ 24 የውድድር ዘመናትን በሊጉ ያሳለፈ ሲሆን፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይ ብራይተን ከብሬንትፎርድ ጋር ባደረገው ጨዋታ የሊጉን የምንጊዜም ከፍተኛ የመጫወት ክብረ ወሰን መስበር መቻሉ ይታወቃል።

በሊጉ 658 ጨዋታዎችን ማድረጉን ስካይ ስፖርት ዘግቧል።

ጀምስ ሚልነር የስንብት ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፥ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 24 የውድድር ዘመናትን ካሳለፍኩ በኋላ፥ አሁን ለተጫዋችነት ዘመኔ ማጠቃለያ ለመስጠት ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ይሰማኛል ሲል ገልጿል።

ሚልነር በልጅነቱ ለሚደግፈው ሊድስ ዩናይትድ በ16 ዓመቱ ተሰልፎ የሊጉ ትንሹ ጎል አስቆጣሪ በሆነበት ወቅት፤ በረጅም የእግር ኳስ ሕይወቱ እንዲህ ዓይነቱን አስደናቂ ታሪክ ይጽፋል ብሎ በፍጹም እንዳልገመተ ገልጿል።

ባለፈው የውድድር ዓመት እግሩን ማንሳት እንኳ እስከማይችልበት ከባድ ጉዳት ደርሶበት የነበረ ቢሆንም፣ በድጋሚ አገግሞ በመመለስ በ40 ዓመቱ ብራይተን በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ለአውሮፓ መድረክ እንዲበቃ ማገዝ መቻሉን በደስታና በኩራት እንደሚመለከተው ተጫዋቹ አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም