ጉጉት ያሸነፈው ቅድሚያ የመምረጥ ዕድል - ኢዜአ አማርኛ
ጉጉት ያሸነፈው ቅድሚያ የመምረጥ ዕድል
የማለዳው ታዳሚ መሆናቸው የአካል ጉዳት የዜግነት ግዴታን ለመወጣት እንቅፋት እንዳልሆነ ያሳዩበት ቀን መሆኑን ይናገራሉ ፤ በምርጫ ጣቢያ ያገኘናቸው ዐይነ ስውሩ አቶ አስረሴ ይርጋ።
አቶ አስረሴ እንዳሉት፤ ወረፋ ሳይጠብቁ ለመምረጥ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ያውቃሉ።
ሆኖም ዕለቱን በጉጉት ሲጠብቁ በመቆየታቸው ሌሊት 11 ሰዓት በመውጣት በምርጫ ጣቢያው ተገኝተው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
በጎንደር ከተማ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው። በከተማዋ ሁለት የምርጫ ክልሎችና 240 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ።
ግንቦት 24ን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በዕለቱ ሌሊት 11 ሰዓት ጀምሮ ወጥተው በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተዋል።
በከተማዋ ሸዋ በር ቀበሌ የሴቶች ወፍጮ የምርጫ ጣቢያ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ መራጮች ድምፅ መስጠት ጀምረዋል።
በምርጫው ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዐይነ ስውሩ አቶ አስረሴ ይርጋም ድምፃቸውን ለመስጠት በዚሁ የሴቶች ወፍጮ የምርጫ ጣቢያ በማለዳው ተሰይመዋል።
በምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ቢያውቁም፣ ጉጉታቸው እንቅልፍ ነስቷቸው ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያው መገኘታቸውን ይናገራሉ።
"የእያንዳንዳችን ድምፅ ዋጋ አላት፤ ለመምረጥ ቀኑን በጉጉት ስጠብቅ ነበር" ያሉት አቶ አስረሴ፤ ድምፃቸውን በመስጠታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ መሆኑን በማንሳትም፣ ሁሉም ዜጋ ድምፅ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
ለሀገር የራስን አስተዋጽኦ ማበርከት ወሳኝ በመሆኑ በምርጫው ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።