ቀጥታ፡

የልጆቻችንን መጻኢ እድል የሚወስነው ታሪካዊ ዕድል ሊያልፈን ስለማይገባ ድምጻችንን ሰጥተናል

ጎንደር ፤ግንቦት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የልጆቻችንን መጻኢ እድል የሚወስነው ታሪካዊ ዕድል ሊያልፈን ስለማይገባ ድምጻችንን ሰጥተናል ሲሉ በጎንደር ድምጻቸውን የሰጡ በዕድሜ የገፉ እናቶች ገለጹ።

በጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት እማሆይ አረጋሽ አለሙ እንደገለጹት እርሳቸው የ80 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ መሆናቸው ሳይገድባቸው በዛሬው ምርጫ ድምጽ በመስጠት በመሳተፋቸው ተደስተዋል።

እድሜዬ ቢገፋም ለነገ ልጆቼ የተሻለች አገር እንድትኖር በመመኘት ለትውልዱ ይበጃል የምለውን መሪ ለመምረጥ በቅቻለሁ ብለዋል።  


 

በእድሜ መግፋት ምክንያት የጤና እክል ቢገጥመኝም ይህ ታሪካዊ እድል ሊያልፈኝ አይገባም በሚል ድምጼን ሰጥቻለሁ ያሉት ደግሞ  የዚሁ ከተማ ነዋሪ እማሆይ አንጓች ካሳ ናቸው።   

ምርጫ ሃገርን የሚያጸና ሠላምን የሚያረጋግጥና የልጆቻችንን መጻኢ እድል የሚወስን በመሆኑ ድምጼን ለመስጠት በቅቻለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም