ቀጥታ፡

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ የማሟላትና የምርጫ ጣቢያዎችን ምቹ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ የማሟላትና የምርጫ ጣቢያዎችን ምቹ የማድረግ ሥራ መከናወኑን በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች ገለጹ።            

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ከማለዳው12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

ኢዜአ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በምርጫ ክልል ስር በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ቅኝት አድርጓል።

የለገሀር ኮንዶሚኒየም ምርጫ ክልል 21 እና 22 አስተባባሪ ትብለጽ ንጉሴ ፤ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁስ ሥርጭት መደረጉን ገልጸዋል።

በምርጫ ጣቢያው ድምፅ ለመስጠት የሚመጡ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ዜጎች ነገ በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሜድሮክ ካርጎና አቪየሽን ሰርቪስ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ምትኩ ፈርሻ በበኩላቸው፤ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ ተሟልቷል ብለዋል።

መራጮችም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያው በመገኘት ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ  እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም